Zellan Patterns Left
Zellan Patterns Right

በቶማስ አድማሱ

ፊልሞቻችንን እወቅሳሁ!

እንዳለመታደል ልበለውና ሰሞኑን በቁጥር ብዙ የሚባሉ የአማርኛ ፊልሞችን ለማየት እድሉን አገኘሁ እና ይህን እንድጽፍ ሆንኩ።

ሲኒማ ዛሬ ዛሬ ዘመን እና ስልጣኔ ቤታችን፣ደጃችን አልፎ ተርፎም እጃችን ድረስ ይዞት ከተፍ አለ እንጂ በባሕርዩ ወደን ፈቅደን ካለበት ድረስ ሄደን የምናየው &ነገ እና ትላንትን ዛሬ ላይ የሚያጋባ ጥበብ ነበረ! ነውም። ከመዝናኛነት ከፍ ሲል ደግሞ ለብዙ ትዳሮች መስመር ምክንያት እንደሆነ የኢትዮጵያ እና የአምፒር ሲኒማ ወንበሮች ያውቃሉ።

ያለማጋነን ፊልሞቻችን ላይ ሰላማዊ ሰልፍ እንድንወጣ በሚያስገድድ መልኩ የታሪክ እና የተዋናይ ድግግሞሽ ይታያል፤ ለመሠረታዊ የፊልም ባህርያት ግድየለሽ መሆንም እንዲሁ።

ጥሩ ፊልሞች መኖራቸውን ባልክድም በቂ አይደሉም እንዲያውም ያንሳሉ እና ፊልሞቻችንን እወቅሳለሁ ብዬ ብዕር ከሰገባ እንድመዝ አስገደዱኝ ፊልሞቻችን ማለቴ ወቀሳ ሰንዛሪ ብቻ ሳልሆን ተቀባይ መሆኔንም ለማሳየት ነውና አንባቢ ያሰተውል፡፡

ቀረጻ፣ ዳይሬክቲንግ፣ ካስቲንግ፣ አክቲንግ በማለት አላድክማቹ ከበጣም ጥቂቶቹ ውጪ ሁሉም ምኑም ውስጥ የሉበትም እኔም ሞያዬ ስላልሆነ አፌን ሞልቼ ልናገር የምችለው እንደ ተመልካች ነውና ይሄን ለባለቤቱ ትተን ፊልሞቹ በሚያስተላልፉት መልዕክት እንወቃቀስ።

ታዋቂው ሜክሲኳዊ ፊልም ሰሪ አሌሃንድሮ ጎንዛሌዝ እንዲህ ይላል “Film making can give you everything, but at the same time, it can take everything from you.” "የፊልም ስራ ሁሉን ነገር ሊሰጥ እንደሚችል ሁሉ በተመሳሳይ ጊዜ ሁሉንም ነገር ሊወስድ ይችላል" እንደማለት ያለ ነው ንግግሩ ፤ ገጸ ባህርይን ከ ተዋናዩ ለማይለይ ማኅበረሰብ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ መገመት ከገብስ ሲቀል ውጤቱ ከጥጥ ይከብዳል እና ፊልማችን ከሰጠን እና ከወሰደብን የቱ ይልቃል? ካደረገብን እና ካደረገልን የቱ ይበዛል? በአጠቃላይ ፊልማችን ማኅበረሰቡን ሰራ ወይስ አፈረሰ ገራ ወይስ አጣመመ?

ፊልማችን ውስጥ ካሉት ባለጸጎች እና በእውን ካሉት የትኞቹ ይበዛሉ? ሰርቶ ጥሮ ግሮ ካለፈለት ወጣት እና የሐብታም ልጅ አግብቶ ኑሮውን ካቀናውስ? ምንድን ነው መልዕክቱ ቆይ አትስሩ ነው? ጥራችሁ ግራችሁ ሐብታም ሴት 'ጥበሱ' ነው?

እፊልሞቻችን ውስጥ መቼ ነው ሴት ከመልኳ በዘለለ የምትወከለው : የሁላችንም እናቶች፣ ሚስቶች፣ እህቶች እና ጓደኞች የተለቀሙ ቆንጆዎች ናቸው እንዴ? እስከ መቼ ድረስ ነው በየ ፊልሙ ላይ ሴት ባለባበሷ ስትወቀስ የምትኖረውስ? ዘመናዊ አለባበሷ የኃጢአት ምልክት ተደርጎ የሚቆጠርባት ዘመን በፊልም ሰሪዎቻችን ልብ መቼ ያከትማል? ሁሏም ሴት የገንዘብ ጥማቷ ከሃቋ ከክብሯ ከስሟ ይበልጥባታል እንዴ ምነው?! ይሄ ጥያቄ ሲመለስ የፊልሞቻችን ፍካሬ ቅርጽ ይይዛል፡፡

መቼ ነው የእናቶቻችን ብርታት የእህቶቻችን ልፋት የሚስቶቻችንን ስቃይ የሚርተክ ፊልም የምናየው!? የተሰራ ካለም ጠቁሙኝ፡፡

ሴት ልጃቸውን የሙት ቃል ለማክበር ብለው ለማታውቀው ሰው ለመዳር ሲያሴሩ የሚያሳይ ፊልምንስ ምን ይሉታል እሺ ? ይሄ እኮ ሃቅ ነው ትሉኝ እንደሁ ሪፓርትና ፊልም ለዩ እላለሁ።

አሁን ከምነግራችሁ አንጻር ከላይ የጻፍኩት ቅብጠት ይመስላል፦

ቆይ ባለቤቴ ካልመታኝ የሚወደኝ አይመስለኝም የምትል ሴት ያለችበት ፊልም ፊልም ነው? ካልተለከፍኩ የዘነጥኩ አይመስለኝም የሚል ስክሪፕት የምትጫወትስ ተዋናይት የምትለው ይሰማታል? ለመለከፍ አይደል የዘነጥሽው ብሎ የሚጽፍ የፊልም ደራሲስ ጤነኛ ነው? ሴትን ሆነ ብሎ ለማሶለድ ብቻ የሚያድን አስቂኝ የወንድ ገጸ ባህርይ መሳል እና በዚያም ላይ ማፌዝ እና ማሳቅ ከሚያስብ ፊልም ሰሪ ይጠበቃል?

ቆይ የመልክ አሳሳላቸውስ ሴት ማለት ፈገግ ያለ መልክ ያላት፣ የሰውነት ቅርጿ የጎላ፣ ሁል ጊዜ ጸጉሯ ተስተካክሎ የተሰራ፣ እሁዷ እና ማግሰኞዋ የማይለይ አድርጎ መሣል እንደው በፈረንጅ አፍ ከተግባባን "ፌር" ነው? ወንድና ሴትን እያሰዳደቡ አዳራሽ ውስጥ ያለ ታዳሚን ማስጭብጨብስ የት ያደርሰናል?

ይቺ ሐገር በሴቶች እንባ፣ ላብ እና ደም እንዳልተሰራች እና እንዳልጸናች ስንት ሴት መምህራን ከዓለም እንዳላስተዋወቁን፣ በእናቶቻችን ምክር ከመከራ እንዳልወጣን፣ ስንት ሴት ሀኪሞች እንዳላከሙን ፊልሞቻችን ግን ሴቶቻችንን "ጎልድ ዲገር" አርገው መሳላቸውስ አያወቃቅስም? እህቶቻችን በየአረብ አገራቱ ተሰደው ያስገጠሙትን በር የወንድም እና የአባት ምሳሌ አድርጎ መሳልስ ያዋጣል? እናት ያበሰለችውን በልቶ በፈረጠመ ጡንቻ ሚስትን መነረትን ያላወገዘ ሲኒማ አይወቀስ የሚል ካለ ይሞግተኝ ፤ እኔ አንድ የቀረ የወር አበባ ተንተርሼ በማህጸን ተኝቻለሁና በእናትህ በማርያም ተባብዬ ጾታ ረስቼ ሰው መሆን ገኖብኝ አድጌያለሁና በልጅነቴ ለሴት ክብር መሞገት አፈወርቅ ሲያሰኝ ተምሬአለሁና እዝነ ወ ዓይነ ሌቡናዬ ለአቅመ ሲኒማ ደርሶ ፊልም ስንመለከት በልቤ ያለችው ሴት አቡጀዴው ላይ ከምትሮጠው ገጸባህርይ አልገጥም ብትለኝ ነው መውቀሴ።

በቅጡ እና በተገቢው ልክ አለመተረክ የጥበብ ጠር እንደሆነ እርግጥ ነው እናም ወደድንም ጠላንም ክብርት ሴትን ደካማ 'ካራክተር' አድርጎ የሚያቀርብ ሲኒማ ሴቶች ሲጠቁ፣ ሲመቱ ፣ሲደፈሩ እና ሲገደሉ አያገባኝም ብሎ በጲላጦስ መንገድ እጁን ቢታጠብ እኔም ወቀሳዬን ጽፌ በነሱው መንገድ በጲሊጦስኛ የጻፍኩትን ጻፍኩ ከማለት ማንም አያግደኝም። ለምን በሉኝ...

ምሳሌ ከሚመሰልለት ነገር እንደሚያንስ ልብ እንበልና በሩዋንዳ ሁቱዎች ቱትሲዎቹን 'ኮክሮች' (በረሮ) ብለው አሳንሰው ከጠሩ በኋላ መግደል አልቀለላቸውም? እንዲያው ነው በየ ፊልሙ ላይ ላልቶ እና ሳስቶ የሴትነት ክብር ሲቀርብ በተመልካች ልብ ምን ይሣላል? ካሚላት ላይ ተንተርሶ ምን ፊልም ተሰራ? (እንደውም አሲድ አስመስሎ ውሃ በመድፋቱ ወንድየው ሲወደስ የአማርኛ ፊልም ላይ እንዳየሁ ትዝ ይለኛል) እግዚኦ!

የሚሰቀጥጠው ደግሞ የእነዚሁ ፊልሞች ገጸባሕርያቱና አዘጋጆች በቀይ ምንጣፍ ተራምደው በሞገስ የአገሪቱን ትልቅ የፊልም ሽልማት ዋንጫ ከፍ አርገው እናቶቻቸውን እና ሚስቶቻቸውን ሲያመሰግኑ ስናይ ነው።

እርግጥ ነው ልቦለዶቻችን ግጥሞቻችን ወጎቻችን ውስጥ ለሴት የሰጠናትን "'ትንሽ' ቦታ" ቢመሰክሩም የፊልም ተደራሽነት ስለሚጎላ ለብቻው ልወቅሰው ወድጃለሁ... ሰሞኑን ወንድ በመሆን እስክናፍር ድረስ ጆሮ ጭው የሚያደርጉ ዜናዎች ስንሰማ ... አንድ አባት ለልጅ ልጁ አባትም አያትም ለመሆን አለማፈሩ ሲነገረን፤ በግ በጠባቂው እንደሚበላ ሁሉ አንዲት ሕጻን የጀግንነት የጠባቂነት ምሳሌዋ በሆነው አባቷ መጠቃቷ ሲተረክ ጊዜ እነዚህ ፊልም ሰሪዎች ከዚህ የሚወጋ፣ የሚያም እና የሚያደማ ታሪክ አጥተው ነው መኪና አጣቢ እና አሳጣቢ የሚያጋቡት እንድል ሆንኩኝ፡፡

ለድርጊቱ በዋናነት የማህበረሰቡ አስተሳሰብ እያደር ማነስ፣ የህጉ ልል መሆን፣ የድህነት ጡንቻ ከአምና ዘንድሮ መፈርጠም እና ሌሎች ነገሮችን እንደ ዋና ምክንያት ብንወስድም ፊልሞች በዝምታቸው እና በግድ የለሽነት አደብዝዘው በሳሉት ሴትነት ምክንያት የድርጊቱ ተባባሪ ናቸው ብዬ ግን መጻፌ እውነት ነው።

እና ምን ይሁን ለምትሉኝ ደረቅ ወቀሳ የፈሪ ነውና መፍትሔ አዘል ትችቴን ጠቁሜ ላብቃ ሴት ሕጻናት በፍራቻ በሚንቀጠቀጡበት እኩል ሰዓት ላይ ሴት ከጥቂቶች በቀር አርቲስቶቻችን ለቲክ-ቶክ ግብአት የሚውል ቪዲዮ ለመስራት ካሜራ ፊት ይውረገረጋሉ፣ ዩትዩበሮቻችን አንዲት ሴት ሺሻ አጫጫሰች(ተግባሩን ባልደግፍም) ለማለት የጮሁትን ያህል ሕፃናት ተደፈሩ ለማለት ይሰንፋሉ ፤ፌስቡክን የሰሞነኝነት አባዜ ውጦታል።

እውነት ነው መቼስ ነፍሳችሁ በስልካችሁ ተብሎ የተረገመ የሚመስለው ትውልዴ የስንፈተ ቁምነገር መድኃኒት ቢያገኝ እላለሁ።

ለዚህ ሁለ ጣጣ ደግሞ የደራሲያን በብዛት ወንድ መሆን ወይም ቅርባቸው ባለች ሴት ዓለሙን መሳል ሲሆን የሴት ተዋንያን እና ፕሮዲውሰሮች ዝንጋኤ ደግሞ የችግሩ ራስ ነው ይህንንም Gender Equality In The Film Industry ብሎ unesco.org ያተመውን ጽሁፍ መመልከት ያንባቢ ሚና ነው፡፡ እናም ህመሙን የሚያውቁ ብዙ ሴት ደራሲያን አያስፈልጉንም ትላላችሁ እስከመቼ ድረስ የሴቶች እንባ ከወንዶች ብዕር ሳቃቸውስ ከወንድ ህሊና ይፈሳል?

ወቀሳዬ ፍረጃ እንዳይሆን ብዬ ከ ሰላሳ በላይ ለስነጽሁፍ እና ለአማርኛ ሲኒማ ቅርብ የሆኑ ሰዎቼን መጠይቅ ብጤ ልኬ ሁለም በኃሳቤ ተስማምተዋል እናም ያልኩትን አሉ እኔም ያሉትን አልኩ ይሄ ይታወቅ!

እርሟን ብታረግዝ ሾተላይ እንደሚያሶርዳት ባልቴት ደና ፊልም ሲሰራ ተሯሩጣችሁ የምትሰርቁ ደግሞ ልቦና ይስጣችሁ።

በመጨረሻ ሴትነት ሲነካ ወዟን፣ እድሜዋን ፣ሳቋን ሽጣ ደስታ የገዛችልኝ የእናቴ ሕመም አጥንቴን ይሰማኛልና ወንዶች ኅሊናችን ይምራን ሴቶች ታናናሻችሁን ጠብቁ እላለሁ!

“FILM MAKING CAN GIVE YOU EVERYTHING, BUT AT THE SAME TIME, IT CAN TAKE EVERYTHING FROM YOU.”

ቸር ያቆየን እና በመልካም ወሬ እንገናኝ!