ይህን ጽሁፍ የምጽፈው ስለጠቅላላው ችግር መፍቻ ለማግኘት የሚረዳ መስሎ የሚታየኝን ኃሳብ በቅንነት ለማካፈል እንጂ የግል ስሜቴን ለመወጫና ራሴን ለማሞኛ አንዳልሆነ ይታወቅልኝ! ዓመታት እና ዘመናት የቀናት ጥርቅም ውጤት ናቸው የእድሜ ዘመናችን ደግሞ በልጅነት ይጀምራል ልጅነት የህይወት ንጹህ ገጽ ነው ዕለት ዕለት አዲሰ ነገር የሚመዘገብበት እና የነገ ማንነት የሚሰፍርበት ባዶ ደብተር፡፡ በሕጻንነት ጊዜ አዕምሮ ላይ የሰፈሩ ነገሮች ሁሉ መቼም ላይፈቁ ይኖራሉ፡፡ እሙን ነው በልጅነት ሁሉ ነገር አዲስ ነውና ልጅነት ክብካቤን ይሻል፡፡ እስቲ ልጅነታችንን እስከቻልነው ድረስ ለማስታወስ እንሞክር ማስቲካ ካልተገዛልን ብለን ያለቀስንበትን ያን ቀን፤ ጓደኞቻችን የያዙትን አሻንጉሊት እንዲገዛልን ብለን ያኮረፍንበትን ያን ዕለት፤ የጎረቤት ሰው ፣ አባታችን ወይም አንዱ የጣለው ሲጋራ ከእጃችን ተገኝቶ የተቆጣንበት እና የተገረፍንበትን ያን ጊዜ እናስታውስ በጊዜው እንዴት ተናደን አሊያም ተከፍተን ነበር? የመከፋት ቀናት ሲጠራቀሙ ክፉ ትዝታ ያላቸውን ቀናት ይወልዳሉ ለዛ ነው ዓመታት የቀናት ጥርቅም እንደሆኑ ማን ይክዳል የምለው እና የጓጓንለትን አሻንጊሊት መቼም የማናገኘው ቢሆንስ ኖሮ? ይባሱኑ የጓጓንለት ያ ማስቲካ እና ያስቆጣንን ያን ሲጋራ በዚያው እድሜያችን አባ እማ ግዙን እያልን ደጅ የምንጠና ቢሆንስ ኖሮ… መሠረት ደሃ በዚያ ላይ የመንግሥት ት/ቤት የምትማር አመዳም ማስቲካ አዟሪ ሴት ናት ፤ 5 ኪሎ ቅድስት ማርያም አካባቢ ከሽሮ ሜዳ ቁስቋም መጥተው ማስቲካ እና ሶፍት እያያዞሩ ከሚነግዱ ጓደኞቿ ጋር ከቀናቸው በባስ ካልሆነ ደግሞ በእግር እየተመላለሱ በመንገድ ላይ የማስቲካ ንግድ ሕይወት ከሚገፉት ውስጥ አንዷ ፤ መንገድ ላይ ዝናብ፡ ብርድ የዉሃ ጥም እና ፀሐይ ከርሃብ ጋር ተደምረው ድህነት የሚል ስም ወጥቶላቸው እንደ ወዳጅ አብራቸው የኖረች ትንሽ ሴት ከ አንድ ሺህ ቀናት በላይ ያዉም። ያለለውጥ 3 ዓመታት ሙሉ በዓላትን ሳታርፍ ክረምት በጋ ሳትል ማስቲካ መቸርቸሯን ሰርታለች 120 ብር ያልተጣራ አማካይ ገቢዋ ነው እና የሷን አፍ ተውሼ አንድ ቀን እዛው አካባቢ ተስፉ ቡና ቁጭ ብዬ ካወጋቺኝን ትንሹን ለማጋራት ወደድሁኝ አስተውሉ መሰረት የ 7 ዓመት ሕጻን ናት። ቅዳሜ ቀን ከምሳ መልስ ቡና እየጠጣሁ መጣችና ማስቲካ ግዛኝ አለች የምትሸጥ ሳይሆን የምትለምን ትመስል ነበር የነጋዴ በራስ መተማመን ፊቷ ላይ የለም እንድትቀመጥ ጋበዝኳትና ያለመግደርደር ቁጭ አለች ጭብርር ያለ ፀጉር ፣ያልታጠበ ፊት እና ቁሽሽ ያለ ጫማ እጥር እድፍ ያለ ልብስ ውስጥ ሰጋጋ የህጻን አንገት ናት መሰረት ማለት እንደተቀመጠች "ምሳ እኮ አልበላሁም" የሚል ድምጽ በድካም ከነጣው አፏ ወጣ… ዶናት በሻይ እያማገች ለምጠይቃት ሁሉ መልስ መስጠት ትታ "እኔ አልከፍልም አደል?" አለቺኝ ድምጿ ሆድ ይበላል 7 ዓመቷ ነው እኔ በ7 ዓመቴ ልጅ ብር እንደማይነካ ብቻ ነበር የማውቀው ይሄኔ እጅግ ገርሞኝ ብዙ ጥያቄ ጠየኳት " ቁስቋምን ታቀዋለህ እዛ ነው ሰፈሬ፡ የምማረው ደግሞ እዚ 'ሚሊሊክ' ማስቲካዬን ከት/ቤት ስወጣ እናቴ ትሰጠኝና እስኪመሽ እሸጣለሁ እናቴ ደግሞ (በእጇ እየጠቆመች) እታች ጋር እጣን ምናምንን ትሰራለች" እያወራች ንቦች ከወረሩት ዶናት ላይ ንቦቹን በትንሿ ጣቷ ገለለ እያደረገች ታወራልኛለች ግማሽ ያክል ሲቀራት "ለብሩክ" ብላ ያዘችው ትንሽ ወንድሟ እንደሚሆን ገምቼ ዝም አልኳት። ብዙ ጉድ አወራችልኝ የከተማችን የመንገድ ላይ የማስቲካ ንግድ ከልመና አይለይም ነዋሪው አምስት ብር አውጥቶ ማስቲካ ከመግዛት ይልቅ አንድ ብር ወርዉሮ ማለፍ ይቀለዋል እዚህ አፍሪካ ውስጥ ማነስ ያሸልማል መውደቅ ያስሞግሳል ከመስራት መለመን እና መስረቅ ሕጋዊ ነው ፤ በጥቁር ሕዝብ ታሪክ የብልትን ጸጉር እያሳዩ ለብብት ጸጉር ማፈር ብርቅ አይደለም። ስለዚህ መሰረት በልመና ዘዬ ማስቲካ ትሸጣለች በየካፍቴሪያው ደጃፍ ቆማ ምሳ እንዳልበላች በሚያስታውቅ ድምጽ ማስቲካ ግዙኝ ትላለች እንደነገረችኝ ከሆነ ይዛ የምትዞረው ማስቲካ ከሶስት ወራት በፊት የተገዛ ነው፤ ማስቲካው ይሸጥም አይሸጥም ቢያንስ 120 ብር ለእናቷ መስጠት የግድ አለባት፤ ልመና የንግድ ልብስ ሲለብስ መሰረትን ይመስላል። መሰረት ሴት ናት (ክብርት ሴት) ፍጥረት እንዲቀጥል የመውለድን ፀጋ ተፈጥሮ ያደለቻት ጽድልት ፍጥረት፡፡ ሰው ሁሉ ሊያደርገው የሚችለውን ልታደርግ የምትችል ሰው ናት መሰረት ይሄ ማለት በመሰረት እና በወንድሟ መሃከል ልዩነት እንጂ መበላለጥ የለም፡፡ መሰረት ታድጋለች ችግሮቿም እንዲሁ አብረዋት ያድጋሉ ያኔ የቤተሰቧ ሆድ እና ተስፋ በሙሉ በትከሻዋ ላይ ይወድቃል እናም ከፍ ላለው ችግር ከፍ ያለ መፍትሄ ስታስስ ሰፊዋ አዲስ አበባ ከቁስቋም አራት ኪሎ ብቻ እንዳልሆነች ይገባታል እና ከቦሌ ፒይሳ እንዳሻት ፣ ከቺቺንያ ካዛንችሽ በፍቃዷ ፣ ብሎም በባንኮክም ሆነ በዱባይ ላይ ያለ ከልካይ እንድትንሸራሸር እግሯ መሃል ያለው ፀጋ ቪዛ ሆኖ እንደሚያገለግላት ሳይገባት ይቀራል? በየ ስፓ እና ማሳጅ ቤቱ ያሉት ሴቶች እኮ ሲወለዱ ጀምሮ ይሄን አይመስሉም ነበር። ይሄን ስል በ መሠረት እና በመሰሎቿ ሕይወት ላይ እያሟረትኩ ሳይሆን ከላይ በጠቀስኳቸው ሰፈሮች ክቡራን ሴቶች ምን ሰርተው ኑሯቸውን እንደሚገፉ አብነት አድርጌ ነው፡፡ ይሄን ደረቴን ነፍቼ መናገር እችላለሁ የትኛዋም ሴት ንጹህ እና ሳቢ ሆና መታየት ከምትሻው በላይ ስለ ገንዘብ ብላ በማታውቀው ወንድ መታቀፍ ያንገሸግሻታል። እና መሰረት ስታድግ በልጅነቷ ዓይኗን እያንከራተተች ማስቲካ እንደምታዞረው ሁሉ ትንሽ ከፍ ስትል እግሯን እያነሳች መኪና እንድታስቆም የፈረደባት ማነው? እሺ መንግሥት ለዚህ ዓይነት ቁም ነገር 'Dirt poor' ነው እንበል የተራድኦ ድርጅቶች አዋጭ ስላልመሰላቸው የመሰረት አይነቶች ከተማውን ሞልተዋል እና እንደ ግልም ዝም ያዋጣል? ’ፌሚኒዝም ’ ይሄ ነው የሚባል ወጥ በአማርኛ ወይም በሌላ የሐገር በቀል ቋንቋ የሚተካው ቃል አለመኖሩ ጽንሰ ኃሳቡ ምን ያህል ሩቃችን እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ለራሳችሁ የ'ፌሚኒስትነት' ማዕርግ የሰጣችሁ ፣ዘናጭ ፣የተማራችሁ፣ 'ሃይሊ ፔይድ'፣ ወንድ ቢል የማይከፍልልላችሁ ሴቶች (እንዲህ አይነት ሴት መሆን በራሱ የሚያስመሰግን እንደሆነ ይሰመርበት) ወይም እንደ እኔ ፌሚኒዝምን የተረዳችሁ ወንዶች ሌላው ቀርቶ ሰብአዊ ነን የምንል ሁሉ፡ መሰረት ካልተደፈረች አሊያ ደግሞ ካልተጠቃች እና ማርች 8 ካልደረሰ ትዝ አትለንም? ወይስ የ “ብርቱካንማ ንቅናቄ” ሰሞን ብቻ ነው ሕመሟ ትዝ የሚለን? በተለየ ደግሞ ይሄ ጽሁፍ የሚመለከታችሁ ፌሚኒስት ከቦሌ ድልድይ- ብራስ ሆስፒታል ድረስ እየተከተለች የምትለምናችሁ መሰረትን ካልረዳ የናንተ ፌሚኒስተነት ምኑ ጋር ነው? አፍሪካ ያውም ኢትዮጵያ ውስጥ ከወንድ እኩል መሆን ቀርቶ እኩል ስለመሆን ማውራት በመገናኛ ብዙሃን ጭምር የሚያሶቅስ አልፎ ተርፎም ስም የሚያሰጥ መሆኑን እና እሱን ታግሎ ለአቋም መቆም የሚያስከብር መሆኑን ባልረሳም እባካችሁ የእውነት የሴት ክብር ብሎም እኩልነት የሚሰማችሁ ከሆነ በየቅርባችሁ ያሉ ሕጻናት ሴት የጎዳና ማስቲካ አዟሪ ሕፃናትን ዕዩ። የፌሚኒዝም ብዙው አስተሳሰብ ቢስማማኝም ሃቅ ሃቁን እናውራ ከተባለ መሠረትን የረሳ ፌሚኒዝም ባፍንጫዬ ይውጣ እላለሁ፤ አንድ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚኖር ወጣት ወንድ ይባስ ብሎም በ መላው ዓለም ይሄ አባታዊው (Patriarchal) ማኅበረሰብ ሴትን ገፍቷል ብሎ እንደሚያስብ ወንድ አንዲት ሴት ላይ አካላዊ ጥቃት በ'ክፉ ወንድ' ሲደርስ ጠብቆ ማኅበራዊ ሚድያን የሚያጨናንቅ ፌሚኒዝም ይቅርብኝ ፤ ስለ ሃቅ እንሙት ካልን እዚህ አገር እነ መሠረትን የረሳ ሴታዊት ንቅናቄ እና እስከ 'Free the nipple' የደረሰ የፌሚኒዝም አስተሳሰብ የራበውን ሰው አረቄ ከመጋበዝ ያለተለየ ጨዋታ ነው። እነ መሰረት ተርበው እና ነገ ለወሲብ አሻንጉሊትነት እንዲሁም ለተራ ሚስትነት ታጭተው ሴት 'ፕሬዘደንት' መሾም እና የትነበርሽ ንጉሤን በየመድረኩ እየጋበዙ ማስደስኮር የክፍለ ዘመኑ ስላቅ ነው። ሃቅ ሃቁን እናውራ ካልን አይቀር ዛሬ የረሳናቸው መሰረት እና መሰሎቿ ነገ የሁላችንም ስጋት ይሆናሉ እና ቢያንስ ዛሬ ሃቅ ሃቁን ለራሳችን እንኳ እንንገረው ብል የሚያሶቅስ አይመስለኝም፡፡ ሴትነት አንድ የተፈጠሮ ቀርፅ መሆኑን ለማወቅ እና በጾታዎች መሃል መበላለጥ እንደሌለ ለመረዳት ብሎም ሴቶች ለመብታቸው መታገል አለባቸው ብሎ ለመናገር ሴት መሆን ግድ አይልም! ሰሞን ጠብቆም ቢሆን ስለ ሴት እኩልነት መታገልም የሚያሶቅስ ተግባርም አይመስለኝም ሴቶች በ መንግሥታዊ የስልጣን ማዕርግ ላይ መውጣታቸውም ልክ ነው (እንደውም ረፍዷል እላለሁ) ግን ከላይ የዘረዘርኳቸው ነገሮች ሁሉ ቢያንስ እንደ ምሳሌ የጠቃስኳት የመሰረትን ሕይወት ካልታደጉ ይሄ ሁሉ ነገር በዜሮ የሚባዛ አይሆንም? ወንዶች በሚሰቶቻችን በእህቶቻችን በእናቶቻችን ጫንቃ ላይ በመንጠላጠል እና በመደግፍ በልጠን ለመታየት ከመሞከር አልፈን የጡንቻን ብልጫ ተጠቅመን ሴትነትን ስንንቅ ስንገፋ እንደኖን እና እንደምንኖር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡መቼስ እሳት እንደሚያቃጥል ሁላችንም ብናውቅም መረዳታችን እንደተቃጠለው ሰው አይሆንም እና ሴቶች (በተለየ ደግሞ ፌሚኒስቶች) ለመሰረት እና ለመሰሎቿ መፍትሄ ልትሆኗቸው ይገባል እላለሁ፡፡ [የዚህ ጽሁፍ የመጀመሪያ አንቀጽ ከ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ “ብቻዬን ቆሜአለሁ” ከተሰኘ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ቃል በቃል ተወሰደ መሆኑ እና የጽሁፉ አጠቃላይ ኃሳብ ለየትኛውም አይነት አስተያየት እና ግሳፄ ክፍት መሆኑ ይታወቅልኝ፡፡]