ዓለማችን ብዙ በሚባሉ የጥፋት መንገዶች ተጉዛ እዚህ እኛ ጋር እንደደረሰች እሙን ነው፤ ኖህ ወይም ሎጥ የሚሉ ስሞችን ስንሰማ ቀጥታ ኅሊናችን የምድራችንን ጥፋት ቶሎ በልቡ የሚስለው ምድራችን ሰንበሯ ቢጠፋም ሕመሟን አልረሳችምና ነው ስለዚህ ዘመን ያመጣውን ፍጡር በትግሉ ወይም በእድሉ ድል እስኪነሳው ድረስ ጭንቀት ፣ስጋት እና ማማረር ከከዋክብት በዝተው ሰማዩን ይወሩታል ፤ እውነት ነው ምንም ያህል መኖር ቢያሰለች እንኳ ሞት በሕይወት ላይ ሚዛን አይደፋም። መኖር በነጻነት የተፈጥሮን ዉበት የማድነቅና የማጣጣም ጉጉት ውጤት ነው። በዘመናዊው ዓለም ከዛሬ ይልቅ ነገ የከበረ ቦታ አለው የበለጸጉት አገራት ገና ላልተወለዱ ልጆቻቸው የሚያቅዱትም ለዚሁ ነው፤ ትላንትና ላይ ሆነን ነገ ያልነው ቀን ነግቶ ዛሬ ሆኖ ስናይ ልባችንን ብዙ ነገዎች ይናፍቁታል፤ ኑሮን በተስፋ ካላማጉት በቀር ያንቃል ፤ ስለዚህ በአዳም ዘር ሁሉ ጆሮ ላይ ሁለት ቃላት ይነግሳሉ መኖር እና አለመኖር ኑሮ የሕይወት እርምጃ (walks of life) ሲሆን ሞት ያለመኖር የበኩር ልጅ ነው። ይህ ሁሉ ዳርዳርታ ዓለማችንን በእኩል ልክ ስለሚያሳስባት 'ኮቪድ 19' ወረርሽን ተጽዕኖ ለማተት የተደረገ ሙከራ ነው ፤ ሰሞኑን ሁላችንም ስለሞት እናስባለን ቢሊየኖች ቤታቸው ሲከትሙ ሚሊየኖች መተንፈሻቸው ሲጠቃ እና እልፎች ዳግም ላናያቸው ሲሄዱ በእውን ማየት ለሁላችንም እንግዳ ነው፤ በእድሜያችን ለመጀመሪያ ጊዜ እውነትም ዓለም እንደጠበበች አመንን፤ አለም ከመጥበቧ የተነሳ ጓቴማላ የተንኳኳ በር ጊንጪ ላይ ይከፈታል ብንል ግነት አይደለም፤ ምክንያቱም ከወራት በፊት ቻይና ብቻዋን ትስለው የነበረ ሳል በቅጽፈት ሁላችንንም የአፍ መሸንፈኛ እንድናድን አደረገ ፤ ትላንት ለ ሐገረ ጣልያን ሲያዝን የነበረ ዓለም አሁን ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ተማጸኖ ቀና አለ፤ የጠዋት ዜናዎቻችን በሞት የታጠኑ ሆኑ፤ ምድርን በሙሉ ያለ ልዩነት የሚያማት ቁስል መጣ። እና መሬት በእኩል ድምጽ 'ኮሮና' 'ኮሮና' ስትል እና የቻለ ሁሉ ቀሳ (Quarentine) ሲገባ ብቸኝነት ሲወረው ወጥቶ መግባት ሲናፍቀው ከዚህ ሁሉ የጥበብ ሰው ምን ያተርፋል ? ለተቀረው ዓለምስ ምን ያበረክታል? የሚለው ጥያቄ የሁሉም ቀልባም ሰው ኃሳብ ይመስለኛል፤አብዛኞቹ የጥበብ ውጤቶች የተመስጦ እና ብቻ የመሆን ልጆች ናቸውና "pen" እና "pain" የድምጽ ብቻ ወዳጅነት ያላቸው አይመስለኝም። ከማኅጸን ብቅ ስንል ጀምሮ አቅፎ ከምድር ያስተዋወቀንን "እጅ" ስንፈራው ስንሸሸው ፤ ከማይታይ ቆሻሻ በየጊዜው ስናጸዳው ባየ ጊዜ ባለ አዕምሮ የጥበብ ሰው ምን ያስባል? ዓለም ስትከደን በሮች ሲከረቸሙ ሞት እና ፍራቻ የምኖዳቸውን እና የናፈቁንን ሰዎች ከማቀፍ ሲያቅቡን እንደ ቀረው ዓለም እሱም ልቡ ይዋልላል ወይስ? ዝምታ (ፀጥታ)ለደራሲ ጆሮ የተፈጥሮ ሽኩሽኩታ ናት ፤ መከርቸም እና በቦታ መታጠር ለገጣሚ መንሳፈፉ ነው። ሞትም ቢሆን ለሃቀኛ ጠቢብ ኢምንት፤ ሃቁን ያወራ እውነቱን የኖረ ስለምን መሞት ይፈራል? የሰዓሊ ዓለሙ ፡ምናቡ፣ ቀለም የራሰ ብሩሹ እና ካንቫሱ አይደሉምን? እዝነ ልቡናችንን የሚንጡ ድንቅ ሙዚቃዎች በሰፊ ኅሊና ነገር ግን በጠባብ ቤቶች ውስጥ አልተቀመሩምን? አፍንጫችን ሞትን ቢምግ ዓይናችን ከኮርኒስ ከፍ ብሎ ባያይ እና የምንሰማቸው ዜናዎች መርዶ ከሟርት ቢደቅሉ፡ የጥበብ ሰዎች ኑሮ ወትሮም ከሕዝቡ ነጠል ያለ ነውና ጠቢባን "ምንተ ንግበር/ምን እናድርግ?" ይበሉ የጥበብ ሰው ብቻውን በሆነ ግዜ ከራሱ ይታረቃል፤ ምን ልስራ ከሚል ተራ ጥያቄ ለምን ልስራው ወደሚለው ማማ ይፈናጠጣል። የሚጽፈው፣ የሚስለው እና የሚዘፍነው ሁሉ ጥቅሙ እና አላማው ይገባዋል ያኔ ወትሮም እንደ ተቃኘ በገና የሆነ ልቡናው ቃል ፣ ፊደል ፣ቀለም እና ዜማ ወደ እጁ ልኮ ያለ ምጥ ጭንቁን እንዲገላገል ይረዳዋል ይሄ ለራሱም ሆነ ለተቀረው ዓለም ጨውነት ነው ይህን አልጫ ጊዜ ማጣፈጫው። ጥበብ ከሁሉ አስቀድማ የተፈጠረች ፣ ከ ህያው ሰው እስከ እጽዋት ድረስ የሚያጣጥሟት ወታደር ከተኩሱ የታመመ ከትራሱ ፋታ የሚያገኙባት ፤ ሞትን ከሚናፍቁ አዕሩግ ገና በማኅጸን እስካሉ ጾታቸው እስካልተለየ ሕጻናት ድረስ እንደ አየር የሚምጓት የምድር እስትንፋስ ናትና የጥበብ ሰው የጸጋው ክብር ገብታው ዓለምን ከአካላዊ መራራቋ ሊያሳርፋት ግዱ ነው። ሊቁ ጸ.ገ.መ አብረን ዝም እንበል በሚለው ስንዱ ሥነ ግጥሙ ሽንጥ ላይ "ከሰው መንጋ ተለይተን ከጠረኑ ተነጥለን ከጉምጉምታው ተገንጥለን ከኳኳታው ብንከለል" ይላል፤ ይኸው ተፈጥሮ በጊዜዋ እፎይታ የሰጠች ሰሞን ሁሉም ወደ ልቡ ወደ ቤቱ ይግባ! የጥበብ ሰው መከለል፣ መገንጠል እና ጽሞና ለተቀረው ዓለም ደስታ ይሰጣልና:: የጥበብ ሰው ብቻውን በሆነ ጊዜ ዓለም ዳግም አብራ ትስቃለች ፤ ሊቁ ሩሚ "እኔ ውስጥ የምታየው ውበት ያንተ ነጸብራቅ ነው" ይላል እኔ ደግሞ ይህን "ጫካ ውስጥ የቆመው ዛፍ ለመኖር ካገዘህ እኔ ቅርብህ ያለሁትማ ምን ያህል እረዳህ ይሆን? ምድር ጫጉላ ላይ ህዝቦቿ ደግሞ ማማረር ውስጥ ነንና ጠቢባን ደመናውን ግለጡ" ጊዜ አልፎ በዚህ ቀን ለመሳቅ ያብቃን።